Back

ታህሳስ 12/2011 ዓ.ም በከተማችን ግልፅ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት እና ተጠያቂነትን በማስፈን የህብረተሰባችንን እርካታ ለማረጋገጥ ተግተን እንሠራለን!

በከተማችን በመልካም አስተዳደር ዕጦት ምክንያት በርካታ ዜጎቻችን እንግልት እያጋጠማቸው እንደሆነ ይታወቃል።በመሆኑም መልካም አስተዳደር የህብረተሰባችን ቁልፍ ጥያቄ፤የከተማ አስተዳደራችን ደግሞ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ሆኗል።

ከተማ አስተዳደራችን በሁሉም አስፈፃሚ ተቋማቱ አማካኝነት የህብረተሰቡን እርካታ የሚያረጋግጡ አገልግሎቶች ለመስጠት ጥረት እያደረገ ቢሆንም፤ህብረተሰቡ በሚፈልገው ደረጃ መልስ ሰጥቷል ለማለት ግን አይቻልም። የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ሁለንተናዊ የለውጥ ሥራዎች ተግባራዊ መሆን ቢጀምሩም እንኳ ዜጐች ከሚያቀርቡት የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ አንፃር ምላሽ ለመስጠት ብዙ መሻሻል የሚፈልጉ ሥራዎች መስራት እንደሚጠበቅበት የከተማው አስተዳደር በውል ይገነዘባል፡፡

ስለሆነም የመልካም አስተዳደር ሁነኛ መገለጫ በሆነው በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የግልፀኝነትና ተጠያቂነት አሰራር በመዘርጋት ቀልጣፋ፣ ፍትሀዊና ውጤታማ አገልግሎት በመስጠት የህብረተሰቡን እርካታ ለማረጋገጥ አስተዳደሩ በትኩረት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

መልካም አስተዳደር የዜጎችን ተሳትፎ የሚያሳድግና ግልጽነትና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ ቢሆንም የነዋሪዎቻችን ፍትሀዊ የልማት ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን መፍታት ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም። በመሆኑም አስተዳደራችን እያደረገ ለሚገኘው ጥረት ስኬታማነት የህብረተሰባችን የተደራጀ ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

የህብረተሰቡ እርካታ ባልተረጋገጠባቸው መስኮች የሚሰጡ የህዝብ አሰተያየት እና ጥቆማዎችን መነሻ በማድረግ በከተማዋ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮች እና ህግን ያልተከተለ ማንኛውንም ድርጊት በነዋሪው ቀጥተኛ ተሳትፎ መታገል ይቻል ዘንድ ከሕዝብ የሚነሱ ጥቆማዎች፣ አስተያየቶችና ትችቶች የሚስተናግዱበት የጥቆማ መስጫ ስልክ መስመሮች ይፋ ሆነዋል፡፡

የጥቆማ መስጫ ማዕከሉ ሙሉ በሙሉ በከንቲባ ጽ/ቤት የሚመራ ሲሆን የከተማችንን ነዋሪ ቅሬታን እና ጥቆማን የሚያጣራ ግብረ ኃይልም ተቋቁሟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከነዋሪው የሚሰጡ ማንኛውም አቤቱታ እና ጥቆማ ከአጣሪ ግብረ ኃይሉ ጋር በመሆን በየዕለቱ ለከንቲባው ሪፖርት የሚያቀርብ ኮሚቴም ተቋቁሟል፡፡

የሕዝብ አስተያየት እና ቅሬታ ተቀባዮቹ ከማንኛውም አካል ነፃ እና ተጠሪነታቸውም ለከንቲባ ጽ/ቤት ሆነው የተደራጁ ሲሆን የሥራ ድርሻቸውም በስልክ ከህዝብ የቀረበን ጥቆማ እና አቤቱታ ለኦፕሬቲንግ ሲስተም አስተባባሪው ማድረስ ይሆናል፡፡

ህብረተሰቡ በከተማችን የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታዎች፣ በህገ ወጥ መንገድ ታጥሮ የተቀመጡ መሬቶች ፣ በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ የኮንደሚኒየም እና የቀበሌ ቤቶች እንዲሁም በአገልግሎት መስጫ ተቋማት እና በመንግስት መስሪያ ቤት ኃላፊዎች ወይም ሰራተኞች በአጠቃላይ በከተማው ውስጥ የሚከናወኑ ማንኛውንም ህግን ያልተከተሉ ሥራዎች ላይ ጥቆማ በመስጠት ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ስለሆነም ህብረተሰቡ ማንኛውንም ቅሬታ ወይም ጥቆማ ሲያቀርብ ፍፁም ከወገንተኝነት ፥ ከቂም-በቀል እና ጥላቻ ነፃ በመሆን ለውጡን ሊደግፍ እና ከተማችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያሳድግ በሚችል መልኩ ለማድረግ የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዲያበረክት የከተማ አስተዳደሩ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ


የአቋም መግለጫዎች ክምችት የአቋም መግለጫዎች ክምችት