ታህሳስ 17/2011 የ2018 የአፍሪካ ታሪክ ሰሪዎች በቢቢሲ

የፈረንጆቹ 2018 ዓመት የመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ እንደመሆናችን ቢቢሲ በድረ-ገፁ በዓመቱ ታሪክ የሰሩ አፍሪካውያን እነማናቸው ሲል አንድ ዘገባ ሰርቷል፡፡
ዘገባው ሰፊ ሽፋን የሰጠው ደግሞ ለኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ነው፡፡
የ42 ዓመቱን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚስትር “የአፍሪካ ወጣቱ መሪ” ሲል የገለፃቸው ዘገባው በተለይ ቤተመንግስት ያለፈቃድ ለመግባት የሞከሩ ወታደሮችን ስፖታዊ እንቅስቃሴ አሰርተው በሰላም መሸኘታቸውን አንስቷል፡፡
በሌሎች ዓለማት እንደዚህ ያለው የወታደሮች እንቅስቃሴ በመንግስት ግልበጣ የሚጠናቀቅ ነበር ያለው ዘገባው ጠቅላይ ሚንስትሩ ግን ሁኔታዎቹን ማረጋጋት የቻሉበት መንገድ አስገራሚ ነው ብሏል፡፡
ወደ ስልጣን ከመጡ ዓመት እንኳን ያልሞላቸው ጠቅላይ ሚስትሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሳካት ይከብዳል የተባሉ ጉዳዮችን በማሳካት ተወዳዳሪ የላቸውም ሲል አሞካሽቷቸዋል፡፡
ቀደም ሲል አገሪቱ በሰብአዊ መብት ጥሰት፣ በመረጃ ነፃነትና ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር በነበራት አለመግባባት በርካታ ቅሬታዎች ከአለማቀፉ ማህበረሰብ ይቀርቡባት እንደነበርም ዘገባው ተጠቅሷል፡፡
ነገር ግን አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ወደ ስልጣን ከመጡበት ቀን አንስቶ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማንሳት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን በመፍታት፣ በስደት ላይ የነበሩ ተቃዋሚዎችንም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ ታግደው የነበሩ ሚድያዎችንና ድረገፆችንም በመክፈት ታሪክ ሰርተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ በአገር ውስጥ ካመጡት ለውጥ በተጨማሪ ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር ሊጠገን አይችልም ተብሎ የነበረውንና ለ2 አስርተ ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን ግንኙነት ወደ ሰላም በመቀየር ዓለምን አስደንቀዋል፡፡
የኢትዮ-ኤርትራን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማስጀመር “ፀሀይን ከምእራብ በኩል እንድትወጣ እንደማድረግ ነው” ሲልም ቢቢሲ የሁኔታውን አይታመኔነት ዘግቧል፡፡
የአገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰምሮ ድንበሮች ተከፍተው የአየር ትራንስፖትና የስልክ ግንኙነት መጀመራቸው ዓለምን አጀብ አሰኝቷል፡፡
ዓለምን ማስደነቅ በዚህ ያላበቁት ጠቅላይ ሚስትር የካቢኔያቸውን ግማሽ በሴቶች በማደራጀት፣ ቁልፍ የመንግስት ሀላፊነቶችን የመጀመሪያዋን ሴት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ለሴቶች በመስጠት ታሪክ መስራታቸውን ቀጥለዋል፡፡
ሌላው የቢቢሲን ቀልብ የሳበው አፍሪካዊ ክስተት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ከስልጣናቸው ወርደው በሴሪል ራማፎሳ መተካት ነው፡፡ አዲሱ ፕሬዝዳንት በአገራቸው ያመጧቸውን ለውጦችም ዘገባው አካቷል፡፡
ለጥቂት ጊዜም ቢሆን የአፍሪካ አገራትን በአንድ ድምፅ ያስቆጣው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ንግግር ሌላኛው ታሪካዊ አጋጣሚ ነበር፡፡
ትራምፕ በንግግራቸው የአፍሪካ አገራትን እንደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳዎች መጥቀሳቸው በወቅቱ ከዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ትችት አሰንዝሮባቸው ነበር፡፡
ባለቤታቸው ሜላኒያ በዚያው ሰሞን በ4 የአፍሪካ አገሮች ጉብኝት እንዲያደርጉ በማድረግ የደረሰባቸውን ወቀሳ ለማለሳለስ መሞከራቸውም ከአመቱ አይረሴ ታሪኮች መካከል ነው፡፡
EBC


ዜናዎች እና ለውጦች ዜናዎች እና ለውጦች